Thu. Apr 25th, 2024

Loading

ሁሉም አማራ ወደ ግንባር እንዲሰለፍ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥሪ አቀረቡ።

በዳንሻ ከተማ ዛሬ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል። የሰልፉ ዓላማ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር ለመስጠት፣ ለሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ደስታን ለመግለጽ፣ አሸባሪውን ትህነግ ማውገዝ እና ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ተብሏል።

ውስጣዊ አንድነትን በማጠንከር የጋራ ጠላትን በብቃት መመከት እንደሚገባ በሰልፉ ተነስቷል። ለዚህም ሕዝቡን መስለው ለጠላት የሚሠሩ አካላትን መምከር ይገባል፤ የማያርፉ ከሆነ ግን ለሕዝቡ ህልውና ሲባል የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተመላክቷል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ "ዛሬ የተገናኘነው ዲስኩር ለማሰማት ሳይሆን የመጣብንን ወራሪ አውቀን የመጨረሻውን ፍልሚያ ለመግጠም ነው" ብለዋል። ኮሎኔሉ አሸባሪው ትህነግ አማራን ለማጥፋት መነሳቱን አንስተዋል፡፡ ይህንን ለመመከትም የአማራ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት አድርጎ በነቂስ ወደ ግንባር እንዲሰለፍ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የህልውና ዘመቻው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ራስን ለመከላከልና ለማስከበር መሰለፍ ይገባል ብለዋል። ለአማራና ለኢትዮጵያ መሞት ክብር ነው ብለን ቀድመን መሰለፍ አለብንም ብለዋል። ኮሎኔል ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ቁርጥ ቀን በመሆኑ ማንኛውም የታጠቀና ትጥቅ የሌለው ኀይል ወደ ማክሰኞ ገበያ፣ ወፍ አርግፍና ሑመራ መክተትና በጋራ ዘምቶ ጠላትን ማሸነፍ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ክብራችንን ስለምንመርጥ ሁላችንም ለሀገራችን መሞት ይገባናል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የሃይማኖት አባቶችም ጦር ግንባር ድረስ ተሰልፈው በጸሎትና በዱአ ሊያግዙ ይገባል ብለዋል። አቅም ያለው ታጥቆ መግጠም ያልቻለ ደግሞ በሞራልና በስንቅ አቅርቦት ሊደግፍ እንደሚገባም አሳስበዋል። በርሃ ያለ ባለመሳሪያ ሁሉ ከነገ ጀምሮ ወደ ግንባር እንዲከትም መመሪያ ሰጥተዋል።

የከተማው ሕዝብ በሰልፉ ላይ "የማንነት ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ መብታችን ነው፤ የአማራ ሕዝብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት አይደራደርም፤ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለፋኖና ሚሊሻ እንዲሁም ለመከላከያ ክብር ይገባል፤ እኛ አማራዎች የምናወራርደው እንጂ የሚያወራረድብን ሂሳብ የለም፤” እና መሰል መልእክቶችን አንግቦ ነው አደባባይ የወጣው፡፡ አስተያየታቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎችም ስለ ክብራቸው፣ ስለ ነጻነታቸውና ስለ ሀገራቸው ሕልውና ሲሉ ግንባር ለመሰለፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሰላማዊ ሰልፉ የዞኑን አስተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች አካላትም ተገኝተዋል።

አሚኮ

Follow us on:

YOUTUBE  FACEBOOK TELEGRAM GOOGLE NEWS TWITTER  INSTAGRAM PINTEREST

Subscribe and Follow us via Email

If you have any comment regarding this article contact us at contact@ethiopianstoday.com

By Chala Dandessa

I am Lecturer, Researcher and Freelancer. I am the founder and Editor at ETHIOPIANS TODAY website. If you have any comment use caalaadd2@gmail.com as email contact. Additionally you can contact us through the contact page of www.ethiopianstoday.com.

Leave a Reply