Mon. Jul 22nd, 2024

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ላይ ካነሷቸው ሀሳቦች የተወሰደ

• ይህ ሰነድ ድርሰት አይደለም፤ማኒፌስቶ ድርሰት መሆን አይችልም፤ከአንድ ዓመት በላይ ዝርዝር ዳታ ሲሰበሰብ ከሙህራን፤ከወጣቶች ከተለያዬ የህብረሰተብ ክፍል ጋር ስንወያይበት ቆይተን ለአምስት ዓመት የምንገባው ቃል ኪዳንና ለአስርዓመት የሚኖረን የብልጽግና ፍኖታችን ተናበውና ተመሳክረው ይችን ሀገር ካለችበት ሁኔታ ወደሚቀጥለው ማሸጋገር የሚችሉ ትላልቅ ሀሳቦች በውስጡ የያዘ ነው፡፡

• ከአንድ ወር በኋላ እኔም የትምህርት ፖሊሲ አለኝ፤እኔም የጤና ፖሊሲ አለኝ የሚል ሀይል ቢኖር ያ ድርሰት እንጂ ፖሊሲ መሆን አይችልም፡፡ፖሊሲ በሰፊ የዳታ ማሰባሰብ፣በመተንተን፣የባለፈውን ችግር በመመርመር መገምገም ከዚያም መማርና ነገን በብሩህ ተስፋ መሰነቅና መንደፍ የሚጠይቅ ስለሆነ እኛ ያዘጋጀናቸው ፖሊሲዎች በብልጽግና የውድድር የተቀመጡ ማኒፌስቶ ሀሳቦች በእያንዳንዱ ዕቅዳችን ውስጥ ያሉ መላው አባላችን የሚያውቃቸው ከህዝባችን ጋር እንደ አስፈላጊነቱ የተወያየንበት ወደፊትም በዚሁ አግባብ እየተወያየን የምናሰፋው የምናሳድገው እንዲሁም የምንተገብረው ሰነድ ነው፡፡

• በደቡብ ብቻ በከምባታ ፣በሀድያ ፣በሀላባ ፣በዳውሮ እንዲሁም በካፋ ዞኖች ከህዝብ ጋር በነበረን ውይይት የሚነሱ ጥያቄዎች የመንገድ፣የጤናና የውሃ ጥያቄዎች ብልጽግና በምን ፍጥነት መመለስ እንደሚችል በተግባር ያሳዬ ድርጅት ነው፡፡ወደ ሰሜን ብንሄድ በተለይ ወሎ ሁለት ዓመታት ብቻ በወሎ ለረዥም ጊዜ የመንገድ ዕጦት ወሳኝ ወሳኝ የመሰረተ ልማት ችግር ያለበትና መልማት የሚሳነው አካባቢ ሆኖ ቆይቶ በብልጽግና ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በወሎ፣ከአፋር፣ ከትግራይ ከተለያዩ ዞኖች የሚያገናኙ እጅግ ለልማት ወሳኝ የሆኑ ለረዥም ዓመታት ሲጠየቁ የነበሩ መንገዶች በሰሜን ሸዋ እንደዚሁ በባህር ዳር ጣናን የሚያሻግርና ከጎንደር ጋር የሚያገናኘው ድልድይ እንደዚሁ በብዙ ቦታ የልማት ጥያቄዎችን በማድመጥ መመለስ የቻለ ፓርቲ ነው፡፡

• ይህንን ልምምዱን አጠናክሮ በሁሉም ዘርፍ የኢትዮጵያን ፍላጎትና የኢትዮጵያን ልዕልና ማረጋገጥ የሚችልበትን አቅጣጫ በነደፈው አግባብ ልክ መስራትና መፈጸም የሚችል ያንንም ማሳዬት የሚችል ፓርቲ መሆኑን በኩራት ለሁላችሁም መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

• ብልጽግና እንደተባለው ለሁሉም በሁሉም ከሁሉም የሆነ ፓርቲ ነው፡፡ብልጽግናን ኢትዮጵያ ውስጥ ማረጋገጥ ከፈለግን ፣ኢትዮጵያን በልዕልና ማማ ላይ ማቆም ከፈለግን፣ኦሮሞም፣አማራም፣ትግሬም ሲዳማም፣ሱማሌም፣አፋርምወላይታም ፣ስልጤም፣ ጉራጌም ሌሎች ህዝቦችም በእኩልነት የሚሳተፉበት፣በእኩልነት የሚጠቀሙበት ማድረግ ካልቻልን ቢበዛ የሃያ አምስት ዓመት ብልጠት እንጂ ዘላቂ ድል ማምጣት አንችልም፡፡

• መላው የብልጽግና አባላት፣መላው የፓርቲያችን ደጋፊዎች መገንዘብ ያለባቸው ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና መውጣት የምትችለው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት፣በፍቅር፣በወንድማማችነት ተከባብረው፣ተፈቃቅደው ተዋደው መትጋት ሲችሉ ብቻ በመሆኑ ተረኝነት ብሎ የሚያስብም፣ተረኝነት ብሎ የሚያውጅም ካለ የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጭር የሚያስቀር ስለሆነ እኛ ብልጽግናዎች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ልብና መንፈስ ተሳስረን ሁሉንም የምንጠቅም፣ሁሉንም የምናገለግል፣ሁሉን የምንወድና ለሁሉም የምንቆም መሆን ይጠበቅብናል፡፡

• በሚቀጥለው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የብልጽግና ማኒፌስቶና እሳቤ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም ዋናው ፍላጎታችን ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ነው፡፡ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ማለት ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ሁሉም በነጻነት የሚሳተፍበት፣በሀሳብ ልዕልና የሚመረጥ ወይንም የሚወድቅበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

• የሚፎካከሩን ፓርቲዎች ከወዲሁ ምርጫ ማሸነፍ ተስፋ ለውም፣ከምርጫ መውጣት ይሻላል ብለው የሚያስቡ ይኖራሉ፡፡ለነሱ ያለኝ ምክር በምርጫ መወዳደርና ሀሳባቸውን መሸጥ ይሻላል፡፡ምክንያቱም እንደከዚህ ቀደሙ አይነት ምርጫ የማድረግ ፍላጎት መንግስትም ብልጽግናም ስለሌለው ለህዝብ በሰተነው ሀሳብና ተስፋ ልክ ህዝባችን መርጦን በፓርላማ በመንግስት በተለያዬ ስፍራ ልዩ ልዩ ድምጾች እንዲሰሙ ማድረግ ከሁሉም ፓርቲዎች የሚጠበቅ ስለሆነ ሁሉም አሁን የሚታያቸውን ችግርና የመሸነፍ ስሜት አሸንፈው በምርጫው እንዲወዳደሩ፤በእኛ በኩል ደግሞ በተቻለ መጠን የትብብርና የፉክክር መንፈስን እንዳናበላሽ፤የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች መታገዝ የሚገባቸውን ነገር ማገዝ ይኖርብናል፡፡


Discover more from ETHIOPIANS TODAY

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

By Chala Dandessa

I am Lecturer, Researcher and Freelancer. I am the founder and Editor at ETHIOPIANS TODAY website. If you have any comment use caalaadd2@gmail.com as email contact. Additionally you can contact us through the contact page of www.ethiopianstoday.com.

Leave a Reply