Fri. Jul 19th, 2024

"ፊቤላ ኢንዱስትሪ 12 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ዘይት አምርቶ ለገበያ አቅርቧል"
– አቶ በላይነህ ክንዴ የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ

ፊቤላ ኢንዱስትሪ በመጀመሪያው ዙር የውጭ ምንዛሪ ተመድቦለት ባስገባው ጥሬ እቃ ተጠቅሞ 12 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ዘይት እና 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተጓዳኝ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ አስታወቁ።

ስምንት ሚሊየን የሚጠጋውን በአከፋፋዮች አማካኝነት ለህዝብ ማድረሱንም አመልክተዋል።

አቶ በላይነህ ክንዴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ፋብሪካው ከተመረቀ ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በመጀመሪያው ዙር የውጭ ምንዛሪ ተመድቦለት ባስገባው ጥሬ እቃ 12 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ዘይት እና 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተጓዳኝ ምርቶች አምርቶ ለገበያ አቅርቧል። ስምንት ሚሊየን የሚጠጋውን ምርቱን በአከፋፋዮች አማካኝነት ለህዝብ ያደረሰ ሲሆን፤ የተቀረውም በመጫን ላይ ይገኛል።

ከአከፋፋዮች ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማዳረስ ችግር ተከስቶ እንደነበር ያመለከቱት አቶ በላይነህ ፣ ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በሃገር አቀፍ ደረጃ 33 አከፋፋዮች ወደዚህ ሥራ ማስገባቱንና፣ ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ለድርጅታቸው የተመደቡ በመሆኑ የስርጭት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ድርጅታቸው በመጀመሪያው ዙር በተፈቀደለት ውጭ ምንዛሪ 14 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይት ከውጪ አስገብቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በላይነህ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 20 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይትና ሌሎች የማሸጊያ እቃዎች ከማሌዥያ አዞ ጅቡቲ ደርሶ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

እስከአሁን የፋብሪካው የዘይት ምርቶች በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በጋምቤላ ክልሎች እየተሰራጩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይነህ፣ ለአካባቢዎቹ የተመደቡ አከፋፋዮች ምርት እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ስርጭቱን በተመለከተ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይነህ፤ ለዚህም መንግሥት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። መንግሥት ለዘይት ቅድሚያ በመስጠት ካለችው የውጭ ምንዛሪ ለዚህ ሥራ መመደቡ ትልቅ ድጋፍ ነው የሚሉት አቶ በላይነህ፤ እኛም የተሰጠንን የተሻለ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ምርታችንን ለህዝቡ እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል።

ምርትን በኃላፊነት ማሰራጨት በራሱ ከባድ ሥራ ነው ያሉት አቶ በላይነህ ፣ይህንን ሥራ መስመር ለማስያዝ ጥቂት መንገራገጭ ሊኖር እንደሚችልና በሚቀጥሉት 15 እና ሃያ ቀናት ውስጥ እነዚህ ሁሉ አከፋፋዮች ወደ ሥራ ሲገቡ ኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ምርቱን ሊያገኝ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፊቤላ እስካሁን ድረስ አንድ ሊትር ከ39.05 እስከ 42 ብር ለአከፋፋዮች እያቀረበ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ በላይነህ፤ ይህ ዋጋ በዓለም ላይ አንድ ሊትር ዘይት ከሚሸጥበት ዋጋ በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል። በማሌዥያም ሆነ በሌሎች አገራት የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ ከአንድ ዶላር በላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ የድፍድፍ ዋጋ ከፍ በማለቱ እና የዶላር ዋጋ በመናሩ፤ በነበረው ዋጋ ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው ያሉት አቶ በላይነህ፤ ከዚህ አኳያ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ አዲስ የትመና ዋጋ እየተሠራለት ነው ብለዋል።

ከጥራት ጋር ተያይዞም የፊቤላ ዘይት ቀደም ሲል ከውጭ ሃገር ታሽጎ ከሚመጣው ዘይት በተሻለ የፋት አሲድን በመቀነስ ለተጠቃሚዎች ምቹ እንዲሆን ተደርጎ እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

ፋብሪካቸው ድፍድፍ ዘይት አምጥቶ በማጣራት ለኅብረተሰቡ በማቅረብ በአንድ በኩል ጥራት ያለው ዘይት ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ መቻሉን ያመለከቱት አቶ በላይነህ፣ በዚህም በዓመት እስከ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪአቸው የዘይት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲችል የጥሬ ዕቃውን በራሳቸው አቅም በሀገር ውስጥ ለማምረት የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው መቀጠላቸውን ያስታወቁት አቶ በላይነህ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው ዓመት በወሰዱት አስር ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አኩሪ አተርና ሰሊጥ ማምረት መጀመራቸውን አመልክተዋል።

ፋብሪካው በቀን አንድ ሚሊየን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ያመለከቱት አቶ በላይነህ ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በየሰዓቱ የሚቆራረጥ በመሆኑ ባለው አቅም ልክ ማምረት እንዳልቻለ አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካው 24 ሰዓት እንዲሠራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት አቶ በላይነህ፤ ከመብራት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። ለአብነትም ሰሞኑን ፋብሪካው ለአራት ቀናት ሥራ አቁሞ እንደነበር አስታውቀዋል።

እንደ አቶ በላይነህ ገለጻ፤ የተሰጣቸው ኤሌክትሪክ መስመር አሮጌ በመሆኑ በየጊዜው ይበላሻል። በዚህ የተነሳ ፋብሪካው በተደጋጋሚ ማምረት ለማቆም ይገደዳል፤ ችግሩ ከዚህም በላይ ለማሽኖቹ ደህንነት ስጋት እየሆነ ይገኛል።

ችግሩን ለመቅረፍና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት 6 ሺ 500 ኪሎ ዋት የሚያመነጩ ትላልቅ ጄኔሬተሮች ገዝተው ማስገባታቸውን ያመለከቱት አቶ በላይነህ ፣ ዕርምጃው ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር በተያያዘ በፋብሪካው ማሽኖች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። አማራጭ ስለጠፋ እንጂ በጀነሬተር በሚገኝ ኃይል ማምረት አዋጭ እንዳልሆነም ገልጸዋል። በኅብረተሰቡ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል።

“ጄነሬተሮቹን ወደ ሥራ ለማስገባት መስመሮች እየተዘረጉ ነው። ከአምስት ቀን በኋላ ወደሥራ ይገባሉ። ይህ ደግሞ ፋብሪካው 24 ሰዓት ሳይቆም እንዲያመርት ያስችለዋል። ይህን ማድረግ ከቻልን በቀን አንድ ሚሊየን ሊትር ማምረት እንችላለን። ይህ ደግሞ ለህዝባችን በበቂ ሁኔታ ምርት እንድናቀርብ ያስችለናል” ብለዋል።

ኢ.ፕ.ድ


Discover more from ETHIOPIANS TODAY

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

By Chala Dandessa

I am Lecturer, Researcher and Freelancer. I am the founder and Editor at ETHIOPIANS TODAY website. If you have any comment use caalaadd2@gmail.com as email contact. Additionally you can contact us through the contact page of www.ethiopianstoday.com.

Leave a Reply